Fana: At a Speed of Life!

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ማዕከል በሳምንት ለ5 ቀናት የጨረር ህክምና እንደሚሰጥ ገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ህክምና ማዕከል በሳምንት ለ5 ቀናት የጨረር ህክምና እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ወደ ሌላ ተቋም በሪፈር የሚልካቸውን ታካሚዎች ችግር መቅረፉንም ገልጿል።

የማዕከሉ ዳይሬክተር ተቀባ ሰንኩርታ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ማዕከሉ አሁን ላይ የጨረር እና የኬሞ ቴራፒ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ከዚህ ቀደም ታካሚዎች ለጨረር ህክምና ወደ ሌሎች ማዕከላት ይላኩ እንደነበር አስታውሰው፤ ከ5 ወር በፊት በተጀመረው የጨረር ህክምና አማካኝነት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሌላ ተቋም መላክ መቅረቱን ተናግረዋል።

በሐኪሞች ትዕዛዝ መሰረት እስከ 35 ቀናት የጨረር ህክምና የሚወስዱ ታካሚዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በሳምንት ለአምስት ቀናት የጨረር ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

አሁን ላይም የካንሰር ህክምና ማዕከሉ በ1 ማሽን በቀን ከ50 እስከ 100 ሰዎች የጨረር ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አቶ ተቀባ ተናግረዋል።

የጨረር ህክምናው ለሲዳማ እና አጎራባች ክልሎች እየቀረበ ሲሆን፤ ከጎረቤት ሀገራትም የሚመጡ ህሙማን መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ታካሚዎች አልጋ ይዘው የኬሞ ህክምና እንደሚከታተሉም ገልጸው፤ ወደሌሎች ተቋማት ሪፈር ይደረጉ የነበሩ የህጻናት እና የደም ካንሰር ህክምናዎችን በማዕከሉ መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ማዕከሉ በስድስት የካንሰር ህክምና ስፔሻሊስቶች እና ባለሙያዎች ተደራጅቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.