የገቢዎች ሚኒስቴር ከሩሲያ ፌዴራል የግብር አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ
አዲስ አበባ ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር እና የሩሲያ ፌዴራል የታክስ አገልግሎት የስትራቴጂያዊ አጋርነት ሥምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
የተፈረመው ሥምምነት የሁለቱን አጋርነት ማጠናከር እና በዲጂታል ታክስ ትራንስፎርሜሽን ልምድን መለዋወጥ እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ሥምምነቱን የተፈራረሙት የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እና የሩሲያ ፌዴራል የታክስ አገልግሎት የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ኤልሲ ባልታ ናቸው።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎቿን ለማስፋት፣ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ እና ለልማት ፈተናዎቿ መፍትሔ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነው።
“ሥምምነቱ የዲጂታል ታክስ ትራንስፎርሜሽን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ገቢን በመሰብሰብ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ያለው ስትራቴጂያዊ አጋርነት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
የሩሲያ ፌዴራል የታክስ አገልግሎት የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ኤልሲ ባልታ የአገር ውስጥ ገቢ የመንግሥታት ዋና የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማሳደግ አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ የሩሲያው ፌዴራል ታክስ አገልግሎት የዲጂታል ታክስ ትራንስፎርሜሽን ያለውን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ፍላጎት እንዳለው ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።