በህገ-ወጥ መንገድ ሁለት ሽጉጥ በመያዝ የተከሰሰው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍቃድ ሳይኖረው በህገወጥ መንገድ ሁለት ሽጉጥ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ይዞ የተገኘው ተከሳሽ በ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ ጌቱ አዱኛ የተባለ ተከሳሽ ላይ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 22 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፉን ጠቅሶ ክስ አቅርቦበታል።
በዚህም፥ ተከሳሹ በሕዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ሸረሮ ከተማ ልዩ ቦታው 03 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ሽጉጥ መያዙን የሚገልጽ ጥቆማ ለፀጥታ አካላት በመድረሱ በቤቱ በተደረገ ብርበራ ሁለት የቱርክ ስሪት ሽጉጦች በቤቱ ውስጥ እንደተገኘበት በቅሱ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ ከደረሰው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን ማለትም ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እንደተገኘበት ገልጾ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ፤ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መስማት ሳያስፈልገው ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።
ከዚህም በኋላ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን መርምሮና ይዞ ተከሳሹን በ5 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
በተከሳሹ እጅ የተያዙት ሁለት ሽጉጦች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑም ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ