አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በሐረሪ ክልል የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በሐረሪ ክልል በልማት ኢኒሼቲቮች የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በክልሉ በከተማና ገጠር የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ጨምሮ በሌማት ትሩፋት በወተት፣ በእንቁላል፣ በማርና በአትክልት ፍራፍሬ ልማት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ያለበትን ሁኔታን ተመልክተዋል፡፡
በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በማሽላና ስንዴ ኢኒሼቲቭ የልማት ሥራዎች የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እያደገ መሆኑን መገንዘባቸውን ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በግብርና ኢኒሼቲቭ በተለይም በማሽላ ምርት ላይ እየታየ ያለው ምርታማነት ለሌሎችም አካባቢዎች በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በትምህርት ቤት ግንባታዎችንና በማህበረሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ የልማት ስራዎችንም ተመልክተዋል፡፡
የሐረር ከተማን ውብ፣ አረንጓዴና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችንና የጀጎል ግንብ ዕድሳትንም መጎብኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡