ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንነት ማደግ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመሳብ አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመላከተ፡፡
ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የተለየ የፋይናንስ ስርዓትን ጨምሮ ከመደበኛ የኢኮኖሚ ህጎች በተለየ ሁኔታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ቦታ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ደረጃ የሚያድጉት ከ50 ሄክታር በላይ የቆዳ ስፋት ሲኖራቸው፣ የካፒታል መጠን ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ መሆን፣ የተፈጥሮ ኃብትን ያገናዘቡ መሆናቸው እንዲሁም በአካባቢው ሰራተኞች መኖራቸውና ሌሎችም መስፈርቶች እንደሚታዩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፓርኮቹ ያሉበትን ደረጃ ገምግሞ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልፀው፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ፓርኮች መካከል መስፈርቱን ያሟሉ 10 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እንዲያድጉ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡
በምንጃር የሚገኘው አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሟሟቱ እና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው አዲስ ኢንዱስትሪ ቪሌጅ የቆዳ ስፋቱ ማነስ ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዳያድጉ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ፓርኮቹን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸውም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካትና በዓለም ዓቀፍ የንግድ ሰንሰለት የሚኖር ቁርኝትን ለማስፋፋት የሚኖረው ሚናም ከፍተኛ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም በቀጣናዊ የንግድ ትስስር ውጤታማና ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ከተሜነትን ለማስፋፋት፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ ቀልጣፋና አመቺ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሁኔታ ለመፍጠር፣ መሰረተ ልማቶችን በተሻለ መልኩ ለማሟላት፣ የቴክኖሎጂና ክህሎት ሽግግርን ለማፋጠንና የሥራ ዕድልን ለመፍጠርም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ማደጋቸው ምርት በጥራትና በብዛት እንዲመረት የራሱን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ገልፀዋል፡፡
ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ማነቆ የሆኑ የህግ ማእቀፎች ካሉ እነሱን በማሻሻል እና ሌሎችንም ስራዎች በመስራት በተሻለ መንገድ የዓለም ሃብት ወደ ኢትዮጵያ እንዲፈስ በቀጣይ እንደሚሰራ ኃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው