በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ልማትን ለማዳረስ አቅም ይፈጥራል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የልማት መርሐ ግብሮችን በቀበሌ ደረጃ ለማድረስ አቅም የሚፈጥር መሆኑ ተመላከተ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በኢሉባቦር ዞን ሀሉ ወረዳ በአቢዩ ኪዳነምሕረት ቀበሌ በአዲሱ አደረጃጀት እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ተመልክቷል።
ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)÷አደረጃጀቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ብሎም በታችኛው አደረጃጀት ያለውን የሰውና የተፈጥሮ ሃብት ለዜጎች ጥቅምና ለሀገር ልማት ለማዋል ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአደረጃጀቱ የተጀመረው ሥራ መልካም መሆኑን ከሕብረተሰቡ ግብረ መልስ ማወቅ መቻሉን ጠቁመው÷በክልሉ ወደ ስራ የገባው አደረጃጀት ወደ ፊት ተገምግሞና ልምድ ተቀምሮበት ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲስፋፋ ይሰራል ብለዋል፡፡
በኢሉባቦር ዞን 13 ወረዳዎች በሚገኙ 287 ቀበሌዎች በአዲሱ አደረጃጀት የተመደቡ ከ1 ሺህ 800 በላይ የቀበሌ አመራር አባላት ስራ የጀመሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
በተራራቁ ቀበሌዎች ተበታትኖ የሚገኘውን የሰው ሃይል አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት ልማትንና ዕድገትን ለማረጋገጥ ቀበሌን ማዕከል አድርጎ የሚሰራ መዋቅር መሆኑን አመልክተዋል።
አስተያየት የሰጡ ቀበሌው ነዋሪዎች በበኩላቸው÷ አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት ለማግኘት ይሄዱ የነበረውን ረዥም ርቀት እንዳቃለለላቸው መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡