Fana: At a Speed of Life!

በላሊበላ ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በላሊበላ ከተማ ሰላምን በጋራ በማፅናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠይቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች በተለይም እንደላሊበላ ያሉ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል።

በመሆኑም የችግር ገፈት ቀማሽ የሆነው የላሊበላና አካባቢው ነዋሪዎች ግጭት ይቁም ሰላም ይስፈን የሚል መፈክር በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።

በሰላማዊ ሰልፉ በመንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ግጭትና ጦርነት ይብቃን የሚል ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላምን በጋራ በማፅናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በመጠየቅም አጋርነታቸው ማሳየታቸውንም ነው ኢዜአ የዘገበው።

በሰላማዊ ሰልፉ፥ ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም፤ ላሊበላ ከተማ ዘላቂ ሰላምን ትሻለች ለዚህም በቁርጠኝነት እንሰራለን፤ ማናቸውም ግጭትና አለመግባባት በጦርነት ሳይሆን በውይይትና በንግግር ሊፈታ ይገባል፤ በተቀደሰው ስፍራ የተቀደሰ ሥራ እንጂ ግጭት ሊኖር አይገባም በማለት ለሰላም ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት አሳይተዋል።

በተጨማሪም ስለህዝብና ስለሀገር ሲባል ችግሮች በንግግር ይፈቱ፤ የከተማችን እስትንፋስ ሰላም ነው፤ ሰላም ቱሪዝም ነው፤ ቱሪዝም ደግሞ ሰላም በመሆኑ ለዚሁ ስኬት በጋራ እንሰራለን ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.