የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መስፈርቱን ለሚያሟሉ አካላት ያለምንም ልዩነት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት መስፈርቱን ለሚያሟሉ አካላት ያለምንም ልዩነት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
አገልግሎቱ ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት ከለላና ጥበቃ ፈልገው ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላና ጥበቃ እየሰጠች እንደምትገኝ ባወጣው መግለጫ ተመላክቷል፡፡
ከነዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኤርትራ የሚመጡ ስደተኞች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተጠለሉ ኤርትራውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለእስርና እንግልት እየተዳረጉ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን ነው አስታውቋል።
“በሀገሪቱ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስርና እንግልት እየተከናወነ ነው” በሚል በሀገር ውስጥና የውጭ ሚዲያ አውታሮች የሚናፈሰው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ገልጿል፡፡
አገልግሎቱ የሚዲያዎቹን ዘገባ ተከትሎ ባደረገው ማጣራት፣ ሕጋዊ የስደተኝነት ዕውቅና ኖሯቸው ለእስርና እንግልት የተዳረጉ ስደተኞች በሀገሪቱ አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡
ስደተኞች የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት ጥሰው ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ የሚኖር ከሆነ፣ አገልግሎቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የሚከታተለው መሆኑንም አገልግሎቱ አሳውቋል፡፡
በሌላ በኩል የስደተኞች ምዝገባ ቆሟል በሚል ሚዲያው የሚያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን አሳውቋል፡፡
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የስደተኝነት መስፈርትን ለሚያሟሉ አካላት ምንም ልዩነት ሳያደርግ የምዝገባ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፤ እየሰጠም ይገኛል ሲል አገልግሎቱ በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል፡፡
ከለላ ለሚጠይቁ አካላት ምላሽ መስጠት የተቀባይ መንግሥት ኃላፊነት እንደመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጥበቃ ለሚሹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በአዋጁ መሰረት እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መርሆዎች መሠረት አድርጎ ተገቢውን አገልግሎት ሲሰጥ ነበር፤ አሁንም እየሰጠ እንደሚገኝ አመላክቷል፡፡