Fana: At a Speed of Life!

ኢጋድ የአንካራውን ስምምነት እንደሚደግፍ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነመንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መንግስት መካከል የተደረሰውን ስምምነት የሚደግፍ መሆኑን ገለፀ፡፡

ስምምነቱን አስመልከቶ የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ በቱርክ አደራዳሪነት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግስት መካከል የተደረሰውን ስምምነት ኢጋድ በአዎንታዊ ጎኑ ይመለከታዋል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል የቆየውን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር እና የሀገራቱን የሁለትዮሽ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡

ስምምነቱ እንዲደረስ ያደረጉትን የሁለቱን ሀገራት መሪዎች ያደነቁት ዋና ፀሃፊው÷ በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት እና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ዲፕሎማሲያዊ ትረቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ እንዲፈፀም የሁለቱ ሀገራት መሪዎችን እንዲወያዩ በማድረግ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢጋድ አባል ሀገራት የሆኑት ኢትዮጵያና ሶማሊያ የደረሱት ተግባራዊ እንዲሆን እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ዘላቂ ትብብር እንዲኖር ኢጋድ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.