በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ለሚያጋጥሙ ጉዳቶች የመድህን ዋስትና ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ለሚያጋጥሙ ጉዳቶች የመድህን ዋስትና መስጠት የሚያስችል ፖሊሲ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ዴስክ ኃላፊ ሃብታሙ ከበደ እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተሳሰብን ባህል ያደረገ ዜጋ ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ ተቀርፆ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ቀርቧል ነው ያሉት።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች በስራቸው ሊደርስባቸው ለሚችል ጉዳት የመድህን ዋስትና እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፖሊሲው በአካታች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሚችሉት የሙያ መስክ በመሳተፍ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል መጥቀም እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።
ፖሊሲው በጎ ፈቃደኞች ላከናወኗቸው ስራዎች ከምስጋና ጀምሮ የሚሰጣቸው የተለያየ ዕውቅና ዋጋ እንዲኖረው የሚያስችል አሰራርን መያዙን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞች በስራ ቅጥርና በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ቅድሚያ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷልም ነው ያሉት፡፡