በጎንደር በ116 ሚሊየን ብር ወጭ የገበያ ማዕከል ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎንደር ከተማ በ116 ሚሊየን ብር ወጪ የገበያ ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል።
የገበያ ማዕከል ግንባታው በጎንደር ከተማ ካሉ የመሠረተ ልማት ችግሮች አንዱ የሆነውን የግብይት ስፍራ ችግር ይፈታል ተብሏል፡፡
ማዕከሉ በ7 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን÷ ግንባታው ከክልሉ መንግስት በተገኘ 58 ሚሊየን ብር እና ቀሪው የግንባታ ወጪ ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢብራሂም ሙሃመድ (ዶ/ር)÷ የገበያ ማዕከል ግንባታው የስማርት ሲቲ ፕሮግራም እና የክልሉ መንግስት በ800 ሚሊየን ብር በ8 ከተሞች የሚያስገነባው አካል ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር እና ፈጣን የግብይት ስርዓት እንዲኖር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የማዕከሉ ግንባታ በአራት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን÷ ግንባታውን የጎንደር ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የማማከር ስራውን ደግሞ የአማራ ልህቀት ማዕከል እንደሚያከናውኑት ተገልጿል፡፡
በበላይነህ ዘላለም