Fana: At a Speed of Life!

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ስልጣን ሊለቁ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተር ክርስቶፎር ሬይ አዲሱ ተመራጭ ዶናልድ ትራምፕ ነጩ ቤተ-መንግስት ከመግባታቸው በፊት ስልጣናቸውን ሊለቁ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ዳይሬክተሩ በፈረንጆቹ 2017 ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ወደስልጣን መምጣታቸው ይታወሳል፡፡

የሥራ መልቀቂያ ውሳኔ ቀላል አይደለም ያሉት ክርስቶፎር ሬይ፥ ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው ውዝግብ ውስጥ ላለመግባት እንደሆነና በተቋሙ ተልዕኮ ላይ ትኩረት እንድናደርግ በማሰብ ነው ብለዋል በሰጡት መግለጫ፡፡

የሎዋ ሪፐብሊካን ሴናተር ቹክ ግራስሊ ኤፍቢአይን ማስተዳደርና መቆጣጠር አልቻሉም በሚል የከሰሱበትን ባለ 11 ገጽ ደብዳቤ ከፃፉ ከሁለት ቀናት በኋላ ዳይሬክተሩ የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚህኛው አስተዳደራቸው ካሽ ፓተልን አፍቢ አይን እንዲመሩ የሾሙ ቢሆንም፥ ይህ ውሳኔ ዴሞክራቶችን ያስማማ ጉዳይ እንዳልሆነም ተሰምቷል፡፡

ሬይ የስልጣና ዘመናቸው ገና ብዙ ዓመታትን ይሻገራል የሚል አቋም ያላቸው ዴሞክራቶች ርምጃውን እንቃወማለን ብለዋል፡፡

የኤፍቢአይ ዳይሬክተሮች ኮንግረሱ ባወጣው ህግ መሰረት እስከ አስር ዓመታት ማገልገል ይችላሉ።

ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት ሃሳብ፥ ባለፈው የምርጫ ቅስቀሳ የተፈጠረውን የጥቃት ሙከራ ጠቅሰው፥ በኤፍቢአይ ተደስቻለሁ ማለት አልችልም ብለዋል፡፡

በሬይ መሪነት ኤፍቢአይ ቤቴን ያለምክንያት ወርሯልረ የሚሉት ትራምፕ፥ በህገ ወጥ መንገድ ክስ እኔ ላይ ለመመስረት ያለመታከት ሞክሯል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም የዳይሬክተሩ የስራ መልቀቂያ ሃሳብ ለአሜሪካ ጥሩ ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስር ገጻቸው አጋርተዋል እንደ አር ቲ ዘገባ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.