ተመድ በጋዛ አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ በእስራኤልና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግና የታገቱ ሰዎች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ የውሳኔ ሃሳብ አሳለፈ።
ይህ የውሳኔ ሃሳብ በ158 ድምጽ ድጋፍ እና በ13 ድምጸ ተዓቅቦ የተወሰነ ሲሆን በጋዛ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስም ይጠይቃል።
የውሳኔ ሃሳቡን አሜሪካ እና እስራኤል ውድቅ ማድረጋቸውን የዘገበው ፍራንስ 24፤ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ በተደጋጋሚ የቀረቡት የውሳኔ ሃሳቦች ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዳያልፉ ሲደረጉ ቆይቷል ብሏል።
በጉባኤው የተነሳው ሌላው ነጥብ የተባበሩት መንግስታት የፍልስጤም ተፈናቃዮች ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ሥራውን እንዲቀጥል እና እስራኤል ያሳለፈችውን እገዳውን እንድታነሳ የሚጠይቅ ነበር።
የውሳኔ ሃሳቡ በ159 ድምጽ ድጋፍ፣ በ9 ተቃውሞና በ11 ድምጸ ተዓቅቦ ተጠናቋል።