የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ሰላማዊ እና ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግስት የተደረሰውን ስምምነት አስመልከተው ባደረጉትንግግር÷ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የጋራ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው እህትማማች ሀገራት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በደም የተሳሰረ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው÷ የሶማሊያ መንግስት አሻባሪዎችን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት በማግዝ ኢትዮጵያውን መስዋዕትነት ከፍለዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በቀጣናዊ ትስስር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንደሚያምን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር እንዲሁም ሰላም እና ዕድገት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን ማከናወኗን አስረድተዋል፡፡
ሰላም እና እገት የቀጣናው የጋራ ፍላጎቶች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በምስራቅ አፍሪካ የሚከሰቱ አለመግባባቶች በቀጠናው የጋራ እድገት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ስምምነት ስታደርግ በጎረቤት ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን በሰላማዊ መንገድ ለማረጋገጥ መሆኑን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር እና ኢኮኖሚ አንፃር የባህር ኮሪደር ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት መንግስት አሸናፊ ያደረገው ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለበርካታ ወራት ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኤርዶኻን ከሀገራቱ ስምምነት ባለፈ በቀጣናው ሰላምን ለማረጋገጥ ያደረጉትን ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አድንቀዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ