ከደንበኞች ሂሳብ ወደ ራሱ ሂሳብ ገንዘብ ያስተላለፈው ተከሳሽ በ14 ዓመት እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከደንበኞች ሂሳብ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ በመቀነስ ወደ ራሱ ሂሳብ ያስተላለፈው ተከሳሽ በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ አባይ ሙሉጌታ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቅፅ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር (2) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀፅ 29 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና (ለ) ስር የተደነገገውን መተላለፉን ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦበት ነበር፡፡
በዚህም በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሽ የአቢሲኒያ ባንክ ሸገር መናፈሻ ቅርንጫፍ ከፍተኛ የቢዝነስ ኦፊሰር ሆኖ ሲሰራ ባንኩ ያወጣውን መመሪያ በመተላለፍ የሂሳብ ባለቤት ወይም ህጋዊ ወኪል አገልግሎት ቀርቦ ሲጠይቅ እና የአገልግሎት ቅፅ ሲሞላ ብቻ መስተናገድ የሚችል መሆኑን የሚደነግገውን መመሪያ መጣሱ ተገልጿል።
በተለይም ከባንኩ 16 ደንበኞች እውቅና ውጭ ከሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተለያየ መጠን በባንኩ የተለያዩ የክፍያ መለያ ቁጥር በማስተላለፍ እና በራሱ መለያ ቁጥር በማፅደቅ ከዛም በድጋሚ እራሱ በኦዲተርነት በማረጋገጥ በአጠቃላይ 592 ሺህ 597 ብር ተቀናሽ አድርጎ ወደ ራሱ ሂሳብ በማስተላለፍና ገንዘቡን ከራሱ ሂሳብ አውጥቶ በመጠቀሙ በባንኩ ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ ተመላክቶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡
ከሳሽ ዐቃቤ ህግ ተከሳሹ ላይ በሌለበት ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶና መርምሮ የጥፋተኝነት ፍርድ በማስተላለፍ በዕርከን 33 መሰረት በ14 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን÷ በዕርከን 10 መሰረት ደግሞ በ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ በመወሰን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሹን በቁጥጥር ስር በማዋል ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ