አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ይኖራታል – አንቶኒዮ ጉተሬዝ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ለማድረግ በቁርጠኝነት አንቶኒዮ ጉተሬዝ አስታወቁ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የስልጣን ዘመናቸው ከመጠናቀቁ በፊት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች እንደሚኖሯት ቃል ገብተዋል።
ዘመነ ስልጣናቸው በፈረንጆቹ 2026 ታህሳስ ወር የሚገባደደው አንቶኒዮ ጉተሬስ በደቡብ አፍሪካ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ለማድረግ በቁርጠኝነት እሰራለሁ ብለዋል፡፡
ከአምስቱ ቋሚ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ሁለት ቋሚ የአፍሪካ አባላት እንዲኖሩ ስምምነት አለን ያሉ ሲሆን፥ በዚህም አሳሳቢው ችግር መወገዱን አብስረዋል፡፡
55 ሀገራት ያሉት የአፍሪካ ህብረት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ውክልና እንዲኖረው በተለያዩ ጊዜያትና በተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በዚህም በፈረንጆች 2005 ሲ-10 በሚል ቡድን በማቋቋም ዋና ተልዕኮውን በፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ ለአፍሪካ የጋራ አቋም ማቅረብ፣ መደገፍ እና ድጋፍ ማሰባሰብ ያደረገ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ህብረቱ በሕንድ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ በይፋ ወደ ቡድን-20 መቀላቀሉ የሚታወስ ነው፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት አሁን ላይ ያለው መዋቅር ጊዜው ያለፈበት ነው በማለት ደጋግመው የሚተቹት ጉቴሬዝ፥ አህጉሪቱ በድርጅቱ ላይ ያላት ውክልና ተቀባይነት እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡
ባሳለፍነው የነሐሴ ወር የፀጥታው ምክር ቤት በኒውዮርክ ባካሄደው ስብሰባ ዋና ጸሃፊው፥ ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የሚያደርግ ማሻሻያዎችን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም በፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይ ኮሚቴው በትኩረት እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፥ አፍሪካ ቋሚ አባል ሳትሆን የዋና ፀሃፊነት ስልጣናቸውን እንደማያጠናቅቁ ያላቸውን ተስፋ መግለጻቸውን አርቲ ነው የዘገበው፡፡