Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የግብርና ውጤት ብዙ የምንማርበት ነው- የናሚቢያ ልዑክ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ብዙ የምንማርበት ነው ሲሉ ፓርላማ አባላት ልዑክ ገለጸ፡፡

የናሚቢያ ፓርላማ አባላት ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ላይ ልምድ ለመውሰድ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ÷ ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚሆን ሰፊ መሬት፣ የእንስሳት ሃብትና ብዙ የውሃ አማራጭ እንዲሁም ለግብርና ልማት ስራ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት እንዳለት ተናግረዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ልማት እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እየተመዘገበ ስላለው ውጤትም ገለጻ አድርገዋል፡፡

የናሚቢያ ፓርላማ ልዑካን ቡድን መሪ ቪንሰንት ማርካ በበኩላቸው ÷ ናሚቢያ በቂ መሬትና ውሃ ቢኖራትም ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በሚገባ ባለመጠቀሟ 80 በመቶ የምግብ ምርቶችን ከውጭ እንደምታስገባ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ብዙ የምንማርበት ነው ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በቀጣይም የናሚቢያ የግብርና ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በግብርናው ዘርፍ ላይ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማየት ልምድ ልውውጥ እንደሚያደርጉም አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.