ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በባቡር መስመር መተሳሰሯን እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በባቡር መስመር መተሳሰሯን እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ እና በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰዉ የተመራ ልኡክ በፈረንሳይ ቫለንሲዬኒስ በሚገኘዉ የአዉሮፓ ህብረት የባቡር ኤጄንሲ ዋና መስሪያ ቤትን ጎብኝቷል፡፡
ከሥራ ጉብኝቱ በተጨማሪም ከተቋሙ ሃላፊዎች ጋር ዉይይት አድርጓል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የኤጄንሲዉ ዋና ዳይሬክተር ጆሴፍ ዶፐልባወር(ዶ/ር) ስለ ኤጀንሲዉ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ሲያብራሩ ፥ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት በድምሩ ከ200 ሺህ በላይ የባቡር መስመር እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
የባቡር አገልግሎት ሰጪዎች በሀገራት ድንበርና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ሳይገደቡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡና የአገልግሎቱ ደህንነት እንዲረጋገጥ ኤጄንሲዉ ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታዎች በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ በኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በባቡር መሰረተ ልማት መተሳሰር የጀመረች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመሰረተ ልማት ትስስሩም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋርም የሚቀጥል በመሆኑ ይህንን የኢኮኖሚ ትግበራ የሚያሳልጥና የሚቆጣጠር ጠንካራ ተቋም መፍጠር ለዘርፉ እድገት ወሳኝ መሆኑንም በአጽንዖት አንስተዋል፡፡