የፈተና አስተዳደር ስርዓቱ የተስተካከለው የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈተና አስተዳደር ስርዓቱን ማስተካከል ያስፈለገው የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና ሀገር የሚረከቡ ዜጎችን ለማፍራት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ÷ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የሚገኘውን ጄነራል ዋቆ ጉቱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ወቅት ÷ በትምህርት ሥርዓቱ የፈተና አስተዳደር ስርዓቱን ማስተካከል ያስፈለገው የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና ሀገር የሚረከቡ ዜጎችን ለማፍራት መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኩረጃ ለጊዜው የሚጠቅም ሊመስል ይችላል ፤ ሆኖም ቆይቶ ራስንም ሀገርንም ይጎዳል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ ኩረጃን የሚጸየፉ በራሳቸው የሚሰሩና የሚተማመኑ ተማሪዎች መሆን እንዳለበቸው አሳስበዋል።
የትምህርት ጥራት እንዲሻሻልና ትውልዱ ሀገርን የመገንባት የወደፊት ኃላፊነቱን በታማኝነት እንዲወጣ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት በትምህርት ዘርፉ እየተከናወኑ መሆኑንም አብራርዋል።
ሀገር ተረካቢ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ አተኩረው እንዲማሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።