Fana: At a Speed of Life!

የትጥቅ ትግል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ከማስከተል ውጭ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትጥቅ ትግል ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን ከማስከተል ውጭ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም ሲሉ የፖለቲካል ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለፁ፡፡

ምሁራኑ የትጥቅ ትግል በኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ታሪክ በተለያዩ ወቅት መሞከሩን አስታውሰው፤ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ማህበራዊ ችግሮችን ከማመጣት ባለፈ ዘላቂ ሰላምን አምጥቶ እንደማያውቅ አንስተዋል፡፡

በኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ ቻን ዮም (ዶ/ር)÷ በትጥቅ ትግል በአብዛኛው የፖለቲካ ግንዛቤ የሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ሰለባ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በተለይም ሴቶች እና ህፃናት ሰለባ እንደሚሆኑ ለኤፍኤምሲ ዲጂታል ገልፀዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የታጣቂ ሀይሎች እንቅስቃሴ እንደሚስተዋል ገልጸው÷ በታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ በሚያደርጉት ግጭት በርካታ ውድመቶች ማድረሳቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከትጥቅ ትግል ይልቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ብቸኛ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ ታጣቂ ሀይሎች ከጠመንጃ ይልቅ ሰላማዊ ፖለቲካን በማራመድ ሃሳባቸውን ማሳካት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

ይህን በመገንዘብ ታጣቂ ሀይሎች ከመንግስት ጋር ስምምነት መፍጠር መጀመራቸው የሚበረታታ እና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ታጣቂዎች እንታገልልሃለን የሚሉት ማህበረሰብ የሚደርስበትን ማህበራዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሰላም ስምምነት ሊመለሱ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

መንግስት ከተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ስምምነት ማድረጉን ያስታወሱት ቻን ዮም (ዶ/ር)÷ ሌሎችንም ወደ ሰላም ለማምጣት ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለበት አመልክተዋል።

ሌላው የዘርፉ ምሁር አቶ ደያሞ ዳሌ÷ የታጣቂዎች ወደ ሰላም ስምምነት መመለስ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልዩነትን በሀይል መፍታት እንደ ባህል እንዳይታሰብ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ልዩነቶች ሲኖሩ በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱን ለማጣጣል የተለያዩ የሴራ ትንታኔዎች እየተሰጡ እንደሆነ አንስተው÷ ፖለቲከኞች ከግል ፍላጎታቸው ባለፈ የሰላምን ዋጋ በመረዳት ስምምነቱን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሰራ በመሆኑ ታጣቂዎች ሃሳባቸውን በምክክር ሂደቱ እንዲያካትቱ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.