Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመጪው ጥር ስራ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከመጪው ጥር ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ እንደሚጀምር የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ኢስማኤል (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ተቋሙ ባለፈው አንድ ዓመት ኩባንያውን እውን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

ገበያው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ሲሆን ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ኃብት እድገት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መጀመር መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አክስዮን የሚሸጡ ኩባንያዎች በየጊዜው የሂሳብ ሁኔታቸው እየተገመገመ ይፋ የሚሆንበት አሰራር ተዘርግቷል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አክሲዮን የሚገዙ አካላት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት ለማከናወን የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ገልፀዋል።

ተቋሙ በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የምጣኔ ኃብትና የፋይናንስ ፍላጎት አማራጭ እንደሚሆንም ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.