ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የልማት ስራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተለያዩ ክልሎች የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ በመኸር አዝመራ በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ማሳን እንዲሁም የወተት ላሞች እርባታ፣ ወተትና ወተት ተዋጽኦ አቅራቢዎች ማህበርን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት÷ ማህበሩ ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በየቀኑ 6 ሺህ 500 ሊትር ወተት በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን የማህበሩ አባላት ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተመራ የአመራሮች ቡድን በአርባ ምንጭ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን ተመልክቷል፡፡
ቡድኑ በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት፣ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የአርባ ምንጭ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም ግንባታ እና በቅርቡ የተመረቀውን የጋሞ አደባባይ ጎብኝተዋል።
በተጨማሪም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን እና የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
በተያያዘ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በአሶሳ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች የዜጎችን ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውን ተመላክቷል።