ፕሬዚዳንት ዳ ሲልቫ በድጋሚ መመረጥ እንደሚፈልጉ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በፈረንጆቹ 2026 በሚደረገው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ለመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡
የ79 ዓመቱ ዳ ሲልቫ በቅርቡ በመታጠቢያ ቤታቸው ወድቀው በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ አደጋ እንዳጋጠማቸው ይታወሳል፡፡
ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸው በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙና ጤንነታቸው መሻሻሉ ሃኪሞቻቸው ያረጋገጡ ሲሆን፥ በደረሰው አደጋም የሚደርስባቸው ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይኖርና በመጪው ሰኞ ወይም ማክሰኞ ከሆስፒታል እንደሚወጡ ተነግሯል፡፡
ይህን ተከትሎም የፕሬዚዳንቱ የማህበራዊ ኮሙኒኬሽን ሴክሬታሪ ፓውሎ ፒሜንታ ፕሬዚዳንቱ በመልካም ጤንነት ላይ እንዳሉ ገልጸው፤ በቀጣይ ምርጫ መመረጥ እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት፡፡
ዳ ሲልቫ ብራዚልን ለመምራት በጥሩ ብቃትና ዝግጁነት ላይ ናቸው ያሉ ሲሆን፥ በዚህም በፈረንጆቹ 2026 ለሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ጠቁመዋል፡፡
በፕሬዚዳንቱ ጤንነት ላይ የሚነዙ አሉባልታዎችንም አጣጥለዋል ሲል የዘገበው ዥኑዋ ነው፡፡