የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን የግንባታ ግብአቶችን እጥረትን በእጅጉ ይቀርፋል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን እና የልህቀት ማዕከል በዘርፉ የሚያጋጥም የግብአት እጥረትን በእጅጉ ይቀርፋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን እና የልህቀት ማዕከልን መጎብኘታቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ሀገራዊ ስትራቴጂክና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽዖ ለማጠናከር የጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም አበረታች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት በተኪ ምርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ዞኑ የማምረት ዐቅሙን በማሳደግ የግንባታ ግብአቶችን እያመረተ መሆኑ በዘርፉ የሚያጋጥም የግብአት እጥረትን በእጅጉ ይቀርፋልም ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የግንባታ ኢንዱስትሪ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተቋማዊና ሀገራዊ ሚናውን ማጠናከርና ዐቅሙን እንዲያጎለብት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።