Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

ጉባኤ በሰላም እንዲካሄድ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከተለያዩ ከ40 በላይ ተቋማት ተውጣጥተው ለእንግዶች አገልግሎት የሚሰጡ ሹፌሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የቱሪዝም ፍሰት እና የባህል ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

ስልጠናው በጉባኤው ላይ የሚገኙ እንግዶች ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጀምሮ እስከ ማረፊያ ሆቴሎች ድረስ ጉባኤው እስኪጠናቀቅ የእጀባ እና የጥበቃ ሥራ እንዲሁም በቱሪዝም መዳረሻዎች ለክብራቸው የሚመጥን የመስተንግዶ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሙያ ቴክኒክ ኮሌጅ የአሽከርካሪ ስልጠና ዲፓርትመንት ኃላፊ ኮማንደር ወ/ሩፋኤል አምባዬ በበኩላቸው ጉባኤው ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ሰላማዊ እንዲሆንና የሀገሪቱን ገጽታ የሚገነባ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ እንደሆነ መናገራቸውንም ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.