Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የህጻናት ጉዳይ የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች የቀጣናውን የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ አጸደቁ፡፡

የፖሊሲ ማዕቀፉ በቀጣናው የሚኖሩ ህጻናት የሚያጋጥማቸውን ችግር በመፍታት ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የአሰራር ማዕቀፎችን የሚዘረጋ ነው ተብሏል።

ፖሊሲው በህጻናት ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ፍትህ፣ የህጻናት ተሳትፎ ማሳደግን ጨምሮ 10 ቁልፍ ጉዳዮችን አካቷል።

በህጻናት ላይ የሚደረግ መገለል፣ የጉልበት ብዝበዛና ሌሎች በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ የሚደረጉ እቅዶችንም የያዘ መሆኑም ተመላክቷል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ፖሊሲው በአባል ሀገራት መካከል ትብብርን በማጠናከር የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ያግዛል ብለዋል።

በቀጣናው የሚኖሩ ህጻናት ለድህነት፣ ለግጭት እንዲሁም በትምህርት ተደራሽ አለመሆንን ጨምሮ ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን በመጥቀስ ችግሩን ለመቅረፍ ትብብርን በማጠናከር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት አንስተዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋትና የትምህርት ቤት ምገባን በመጀመር ህጻናት በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚረዱ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢጋድ የጤና እና ማህበራዊ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ፈትያ አሉዋን በበኩላቸው÷ ኢጋድ ለሰላም፣ ማህበራዊ ደህንነትና ምጣኔ ሃብት እድገት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

ለእነዚህ ጉዳዮች መሳካት የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህጻናት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው÷ ለዚሁ ስኬት የፖሊሲ ማዕቀፉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

የደቡብ ሱዳን የስርአተ-ጾታ፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አያ ቤንጃሚን ሊቦ (ዶ/ር) እና የኡጋንዳ የህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ባላም አቲንይ (ዶ/ር) ለቀጣናዊ ችግር መፍትሄ ለማምጣት ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የሌሎች አባል ሀገራቱ ተወካዮችና አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለፖሊሲ ማዕቀፉ ተግባራዊነት በትብበር እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.