በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች ቡድን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ላይ ተወያይተዋል።
በመድረኩ ሀገራዊ ምክክርን በውጤታማነት ለማከናወን፣ የሽግግር ፍትህን ለመተግበር እና በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ዘላቂ ልማትን ለማምጣት እና ሰላምን ለማስፈን መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለዘላቂ ልማት መሰረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሰላም መፈጠሩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ የአካባቢ አስተዳደሮችን ወደ ስራ እንዲመለሱ እና ለቀጣይ የመልሶ ግንባታ ጥረቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚገኝበትን ደረጃ በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ ግልጽ እና ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች 964 ወረዳዎችን ተሳታፊ ማድረጉን ገልጸዋል።
የሎጂስቲክስ ጉዳዮች፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች እና ውስን የህዝብ ተሳትፎ በምክክሩ ላይ ፈተና ቢሆኑም እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ጠንካራ የማህበረሰብ ተሳትፎ እና ግንኙነት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርአያስላሴ በሰጡት ማብራሪያ ፖሊሲው በወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነት ፍለጋ፣ ተቋማዊ ለውጥ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች በመንግስት የስራ ሀላፊዎች ገለጻ በማድረግ ከልማት አጋሮች ጋር ውይይት እንደተደረገባቸው እና በቀጣይ እርምጃዎች ዙሪያም ምክክር መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።