Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር …

አዲስ አበባ፣ ታሕሳሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት መነቃቃት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የራሷ ወደብ እንደሌላት ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ሕብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።

ይህን የአንካራ ስምምነት ተከትሎ የሕግ ባለሙያው አንዷለም በእውቀቱ÷ ኢትዮጵያ ሰሞኑን ከሶማሊያ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ከዓለም አቀፍ ሕግ አንጻር ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በአፍሪካ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት ሕዝብ 33 በመቶውን እንደሚሸፍን በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች የ2024 ሪፖርት ያመለክታል ብለዋል።

ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ገናና ሀገር የነበረችው ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ የነበራትን የባሕር በር ማጣቷንም አውስተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የቀጣናው ቁልፍ እና በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በዘላቂነት የራሴ የምትለው የባሕር በር አጥታ ወደ ጎረቤቶቿ ለማማተር መገደዷን ነው የጠቀሱት፡፡

በአንካራው ስምምነት ሁለቱ ሀገራት በወዳጅነትና የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት መስማማታቸውን በማድነቅ ትክክለኛ መነገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በቨርሳይ ስምምነት ፈረንሳይ፣ ብሪታኒያ፣ አሜሪካና ወቅቱ ሶቪዬት ሕብረት የኤርትራ ዕጣ ፈንታን ሲወስኑ የኢትጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ አቋማቸውን ማንጸባረቃቸው ለጉዳዩ የሰጡትን ትኩረት ያሳያል ነው ያሉት፡፡

የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ ሀገራት ዕውቅና እንደሚሰጡም ተገልጿል፡፡

በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋራ በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።

ይህን ስምምነትም የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግፈውታል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.