ሚኒስትሮቹ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሮች በተለያዩ ክልሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በቡታጅራ ከተማ የሚገኘውን የደስታ ጋርመንትን ጨምሮ በመስቃን ወረዳና በቡታጅራ ከተማ በግብርና ሥራዎች የተሰማሩ ወጣቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክቷል።
እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በሌማት ትሩፋት ሥራ የተሰማሩ ወጣቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡
በወረዳው በሌማት ትሩፋት የተሰማሩ ሰዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ለገበያ በማቅረብ የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ የተለያዩ የግብርና የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም 18 ሺህ ሔክታር የተፈጥሮ ቀርቀሃ ደን ሃብትንና የቦንጋ እንስሳት እርባታን መመልከታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እና የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በዲጂታል ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በርካታ እና አበረታች ቢሆኑም በቀጣይ እንደ ሀገር ሰፊ ሥራ ይጠበቃል፡፡
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን በቴክኖሎጂ መደገፍና ዲጂታላይዝ ማድረግ ወቅቱን የዋጀ ሥራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በተመሳሳይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም በሰሜን ቤንች ወረዳ በቡና ልማት እንዲሁም በሚዛን አማን ከተማ በተለይም በሌማት ትሩፋት የተከናወኑ ተግባራትን ተመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ጉብኝታቸውን በመቀጠል በተለያዩ ወረዳዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን የሚመለከቱ ይሆናል፡፡
በዘላለም ግድ የለው