ማህበሩ እየሰጠ ያለውን ሰብዓዊ አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል አለበት- ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ማኅበሩ እየሰጠ ያለውን ሰብዓዊ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እየሰጠ ያለውን ሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽነት ማጠናከር እንደሚገባው የማኅበሩ የበላይ ጠባቂና የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አሳሰቡ፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር 20ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
ፕሬዚዳንት ታዬ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ላለፉት 90 ዓመታት ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ማኅበሩ የሰጠው ሰብዓዊ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ማኅበሩ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችለው ቁመና በሂደት መገንባቱን ገልጸው፥ የቀጣዩንም ታሳቢ በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ አገልግሎቶች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈጣን ድጋፍና እገዛ በማድረግም ኃላፊነቱን የመወጣት ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ በበኩላቸው፥ በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ ለሚሆኑ ሰዎች የሕይወት አድን ሥራ ከማከናወን በተጨማሪ ዘርፈ-ብዙ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ያለፉት ሦስት ዓመታት የማኅበሩ ዓመታዊ ገቢ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም ለ16 ሚሊየን ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ እንዲሁም በአደጋ ሥጋት ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ሥራ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
መንግሥት ለማኅበሩ በየዓመቱ ሲያደርግ የነበረውን የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ወደ 10 ሚሊየን ብር ማሳደጉንም ጠቅሰዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙት ከ80 በላይ የመድኃኒት መደብሮች አማካኝነት በዓመት 3 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እያቀረበ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡