የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ የተለያዩ ውሳኔዎች አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚህም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለማሻሻል በወጣ ደንብ ዙሪያ ተወያይቶ አስተያየትና ግብዓቶችን በማከል ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል።
በተጨማሪም የመጠባበቂያ ፈንድ አሰባሰብና አተገባበር መተዳደሪያ ደንብ ላይ በመወያየት፤ ደንቡ በተለያየ ጊዜ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን በራስ አቅም ለመቻል እንደሚያግዝ በመወያየት ግብዓቶችን በመጨመር አፅድቆታል።
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህግ ታራሚያዎች አያያዝ እና አስተዳደር ደንብ እንዲሁም የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ፖሊስ አባላት ስነ-ምግባር እና መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተወያይቶ እንዲጸድቅ ወስኗል።
በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ዙሪያ የተወያየው ካቢኔው፤ የኮሪደር ልማቱ እድገት ከማፋጠን ባሻገር ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹና ፅዱ ለማድረግ ድርሻው የጎላ በመሆኑ ልማቱን ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።