በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ42 ሚሊየን በላይ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ42 ሚሊየን በላይ ለማድረስ ማስቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር)÷ ባለፉት አራት አመታት በነበረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የቴሌኮም ዘርፉ ለግል ባለሃብቶች ክፍት መደረጉንና የ10 በመቶ ድርሻውንም ለአክስዮን ሽያጭ እንዲቀርብ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ይህም ዘርፉ በፍጥነት እንዲያድግና ተደራሽ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው÷ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ17 ሚሊየን ወደ 42 ሚሊየን በላይ እንዲደርስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ስትራቴጂው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ጨምሮ በመንግስት እና በግል የሚገነቡ የዳታ ማዕከላት ቁጥርን ለማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም የኃይል አቅርቦትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት መጨመሩን አስገንዝበዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በአይሲቲ ፓርክ ትላልቅ የመረጃ ማዕከላት መገንባቱን እና ማዕከላቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በፓርኩ ባለፉት አራት አመታት በተከናወኑ ተግባራት ለኢንቨስትመንት፣ ለስራ እድል ፈጠራ፤ ተሰጥኦን ለማበልፀግና ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችሉ ምቹ መደላድ ተፈጥሯል ብለዋል።
በተጨማሪም ሚኒስቴሩ የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያን ኮደርስ መርሃግብርን ጨምሮ ዲጂታል ክህሎት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር በርካታ ተግባራትን እያከከናወኑ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡