የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትብብር ያጠናክራል – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ዘመናትን የዘለቀ ወንድማማችነት የሚያጠናክር ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻድሊ ሀሰን ገለፁ፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰውን የአንካራ ስምምነት ተከትሎ ከክልሉ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በምክክር መርህ የመፍታት ባህሏን ለዓለም ያሳየችበት መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ እንደሀገር የተጀመረውን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያግዛል በማለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራዎችን መስራት መቻሏን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፍላጎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአንካራው ስምምነት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ዘመናትን የዘለቀ ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክርእና የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ስምምነቱ የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና የማይዋጥላቸው እና ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ለማስገባት ሲታትሩ የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን አንገት ያስደፋ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ መግለፃቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡