370 ኪሎ ዋት ማመንጨት የሚችል የሶላር ኃይል ማመንጫ ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ195 ሚሊየን ብር ወጪ 370 ኪሎ ዋት ማመንጨት የሚችል የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር)÷ ለ15 ሺህ የገጠሩ ማህበረሰብን ንፁህ ኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ለመብራት፣ ለማብሰያ፣ ለግብርናና ለከተማ ውስጥ አገልግሎት የሚውል ትልቅ ፕሮጀክትና ለአካባቢው ማህበረሰብም የስራ ዕድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ባለፉት አመታት በኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆኑን ገልፀው ፕሮጀክቱ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚከናወነውን የልማት እንቅስቃሴ ይደግፋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው ÷የአካባቢው ህብረተሰብ ያገኘውን የመብራት አገልግሎት በዘላቂነት ለመጠቀም በአግባቡ እንዲጠብቅ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ወላቡ ወረዳ ኦቦርሶ ከተማ የተመረቀው ፕሮጀክቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ያሰሩት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።