በኦሮሚያ ክልል በመኸር እርሻ 110 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከለማው ሰብል እስከአሁን 110 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ በሪሶ ፈይሳ÷ በክልሉ በመኸር እርሻ ከ10 ነጥብ 85 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ገልጸው ከዚህም 337 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ከሚገኝና ለመሰብሰብ ከደረሰ ሰብል ውስጥ እስከ አሁን 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል መሰብሰቡንም ጠቁመዋል።
በዚህም 110 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ያሉት ሃላፊው በክልሉ 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም እርሻ የአስተራረስ ዘዴ መታረሱን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምርት ብክነትን ለመቀነስ የምርት አሰባሰቡ በማሺነሪዎች በመታገዝ እንዲከናወን መደረጉን አንስተው ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች፣ በአርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በከፊልና በቆሎ በሚመረትባቸው ምዕራብ የክልሉ ዞኖች ምርት እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።