ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የልማት ስራዎች ጉብኝት እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በክልሎች እያደረጉት ያለው የልማት ስራዎች ጉብኝት እንደቀጠለ ነው።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የአዘዞ ጎንደር የአስፓልት የመንገድ ስራ ያለበትን ሂደት ተመልክተዋል።
እንዲሁም በጎንደር ከተማ በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ያሉ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን÷በቀጣይም ሚኒስትሩና ሌሎች የሥራ ሀላፊዎች የፌደራል ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ይጎበኛሉ።
በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በጉብርዬ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ፣ የከተማ ግብርና እና ሌሎች የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽም መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ(ኢ/ር) ምስራቅ ዕዝ ያከናወናቸው እና እያከናወናቸው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች እና የዕዙ አጠቃላይ የግዳጅ አፈፃፀምን ተመልክተዋል።
አይሻ መሃመድ(ኢ/ር) በዚሁ ወቅት÷ምስራቅ ዕዝ በአነስተኛ በጀት በአጭር ጊዜ ያከናዋናቸው በርካታ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ለሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጭምር ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ሃላፊዎች ቡድን በጋምቤላ ክልል አኝዋሃ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
በምናለ አየነው