የመስኖ ፕሮጀክቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተለያዩ ክልሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከሲዳማ ክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የተገነባውን ጋሎ አርጌሳ የመስኖ ፕሮጀክት የልማት እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅትም የመስኖ ፕሮጀክቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ሚኒስተሯ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት መሠረተ ልማቶችን ለመገንባትና ለማስተዳደር እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ በባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተመራ የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በጋሞ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ሲያካሂድ የቆየውን የድጋፍና ክትትል ሥራ አጠናቅቋል።
ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ እንዳሉት ÷የከተማ ኮሪደር ልማትን በሌሎች ከተሞች ከማስፋት ባለፈ ለገጠር ኮሪደር ልማት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭ ከተማ ዙሪያና በምዕራብ አባያ ወረዳ እንዲሁም በጨንቻ ከተማ ዙሪያ ወረዳ እየተከናወኑ ያሉ የሌማት ትሩፋትና የልማት የፕሮጀክቶች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረዳታቸውንም አንስተዋል፡፡