Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች በገላን ጉራ ሳይት የ60 ሺሕ ቤቶችን ግንባታ ሒደት ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ሒደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በአዲስ አበባ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት እየተገነቡ ያሉ የቤት ግንባታዎችን መጎብኘታቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም የኦቪድ ገላን ጉራ ሳይት 60 ሺሕ ቤቶች ግንባታ እና በለገሀር ጊፍት ሪልስቴት የሚገነባቸውን የ 4 ሺህ 370 ቤቶች ግንባታ ሒደት መመልከታቸውን ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም በቦሌ ሩዋንዳ በግሉ ዘርፍ እየለሙ የሚገኙ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ሒደት ተዘዋውረው መመልከታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኦቪድ ገላን ጉራ ሳይት ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የሚሆኑ 770 ደረጃቸውን የጠበቁ ምትክ ቤቶችን ቅድሚያ በመስጠት ግንባታቸው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በገላን ጉራ ፕሮጀክት ከሚገነቡ ቤቶች ውስጥ ኮንዶሚኒየም በመቆጠብ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ በመመቻቸት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የተጀመሩ ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.