በመዲናዋ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
በፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የተመራ የፌዴራል ሱፐርቪዥን ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የሪፎርምና የልማት ስራዎችን አፈፃፀም ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፣ በሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ በመሬት ልማትና አስተዳደር እንዲሁም በተለያዩ ክ/ከተሞ ችየተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷በአዲስ አበባ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይም በሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ እና በመሬት ልማትና አስተዳደር የመጣው ለውጥ አበረታች ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬትን እንደሃገር የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግና በከተማዋ እሮሮ ይበዛበት የነበረውን የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮን እንዲሁም የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲን በአሰራር ለማዘመን የተሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸው የሚዛን ቡና ቅምሻና ሰርትፊኬሽን ማዕከል፣ የሚዛን አማን ዱቄት ፋብሪካንና በግል ባለሀብት በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሙፍቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለስኬታማ ድል የበቃችው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት በመተግበሯ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ኢትዮጵያ በ2024 በጠቅላላ ሃገር ውስጥ ምርት ኢትዮጵያ ከአምስቱ የአፍሪካ ምርጦች ውስጥ አንዷ ሆና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መመረጧን አስታውሰዋል።
ለዚህ ስኬታማ ድል የበቃችውም ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለየኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት መተግበር በመቻሏ ነው ብለዋል።