የግብርና ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
የክልሉ የግብርና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ሽግግር ፎኖተ ካርታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚሁ ወቅት÷ በክልሉ ያሉትን የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሀይል በማቀናጀት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተጀመሩ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ኢኒሼቲቮችን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በመተግበር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ያለውን እምቅ የተፍጥሮ ፀጋዎችን ወደ ላቀ እድገትና ብልፅግና ለማሸጋገር የተጀመረው ክልላዊ የግብርና መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን ድርሻው የጎላ እንደሆነም መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ ያሉ አቅሞችና ጸጋዎችን ለይቶ የማልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማምጣት እስካሁን ለአራት ክልሎች የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።