የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን የምናጠናክርበት ነው – አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች የምናጠናክርበት ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለፁ።
ለ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤና ለ46ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ቅድመ ዝግጅት የበጎ ፈቃድ ፕሮቶኮሎችና የመሪ ባልደረቦች ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በስልጠናው መክፈቻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፥ ኢትዮጵያ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያካሄደች ነው ብለዋል።
ጉባዔው ኢትዮጵያን ይበልጥ ከማስተዋወቅና ገፅታን ከመገንባት ባለፈ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የምናጠናክርበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ተመራጭ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማስፋት ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሳደር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ለጉባዔው ይህን የሚመጥን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በአዲስ አበባ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ይካሄዳል፡፡
የካቲት 8 እና 9 ቀን ደግሞ 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እንደሚካሄደ አስታውሶ የዘገበው ኢዜአ ነው።