የሀገር ውስጥ ዜና

በ19 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወጪ 12 መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈረመ

By Tibebu Kebede

July 22, 2020

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ19 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወጪ 12 መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል የውል ስምምነት ፊርማ ከተቋራጮች ጋር ተፈራርሟል።

የስምምነት ፊርማ የተከናወነባቸው 12ቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች በድምሩ 825 ነጥብ 23 ኪሎ ሜትር ርዝመት አላቸው።

ለግንባታው ከሚያስፈልገው ወጪ መካከል የአሥሩ መንገዶች በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ሲሆን የሁለቱ መንገዶች ግንባታ ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን ነው ተብሏል።

የውል ስምምነቱን ከፈረሙት የሥራ ተቋራጮች መካከል ስድስቱ ሃገር በቀል ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ዓለም አቀፍ የውጭ ተቋራጮች ናቸው።

መንገዶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወራት እስከ አራት ዓመት እንደሚወስዱ ተጠቁሟል።

መንገዶቹ በገጠር እስከ 10 ሜትር በከተማ ደግሞ ከ10 ሜትር በላይ እንዲሁም በመንገዶቹ ላይ ድልድዮች እና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎች ይኖራቸዋል ተብሏል።

ስምምነት የተደረገባቸው መንገዶች ከነቀምቴ ቡሬ፣ ከጎዴ ሀርገሌ፣ ከደምበጫ አዴት፣ ከሳውላ ማጂሎት፣ ከቡልቡላ አላጌ፣ ከጊንባ ተንታ መገንጠያ፣ ከአላባ ዱራሜ መገንጠያ፣ ከሀይቅ ጭፍራ፣ ከያሶ ቻግኒ፣ ከሜሎዶኒ መገንጠያ ቡሬ እንዲሁም ከደብረታቦር ጉና ናቸው።

በአክሱማይት ገብረህይወት