Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ርዋንዳ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ርዋንዳ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ መረጃ በመለዋወጥ በጋራ ለመከላከል ተስማሙ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና የርዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ ናቸው፡፡

በሀገራቱ የፖሊስ ተቋማት ያሉ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች አቅሞችን በመጠቀም በተለይ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና በርዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ አካዳሚ ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ለማሰልጠን ብሎም ልምድ ለመለዋወጥ መግባባታቸውን ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የፖሊስ ትብብር መድረክን በጋራ ለማጠናከር እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ ባለፈ እንደ አፍሪፖል ያሉ ተቋማትን በማጠናከር በጋራ ለመሥራት ተነጋግረናል ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡

በ2025 በሚካሄደው የኢንተርፖል ፕሬዚዳንት ምርጫ ላይ እንደ አፍሪካ እጩ ተወዳዳሪ በጋራ ለማዘጋጀት እና የሀገራቱን የፖሊስ ተቋማት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መስማማታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ስምምነቱ በቅርቡ ወደ ተግባር እንዲቀየርም ከሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የተቀናጁ ቴክኒካል ቲም መደራጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ በበኩላቸው የትብብር ስምምነት ማዕቀፉን ለመተግበር ተቋማቸው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ማዕቀፉ የሁለቱ ሀገራት ደኅንነት ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ከማበርከቱ ባለፈ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብሎም ለዓለም የድርሻውን ሚና እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.