Fana: At a Speed of Life!

ኪርጊስታን የአንካራ ስምምነት መረጋጋትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው አለች

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኪርጊስታን በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል የተደረገው የአንካራ ስምምነት መረጋጋትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው ገለጸች፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከተሾሙበት ኪርጊስታን ሪፐብሊክ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሆኑት ተምሪበክ ኢርክኖቭ የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጅ ባቀረቡበት ወቅት ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት አምባሳደሩ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ስምምነት ሀገራቱ ልዩነትን ወደጎን በመተው በመከባበር፣ በወንድማማችነትና በወዳጅነት ስሜት ለጋራ ብልጽግና ብሎም ለቀጠናው ዘላቂ ጥቅም መጠበቅ በስኬት መጠናቀቁን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ እንዳላትም ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም ማሳያ በሰላማዊ መንገድ የተከናወነው ታሪካዊው ስምምነት የሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም በትብብርና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን፤ ኢትዮጵያ በቀጠናው ለዘመናት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ መሰማራቷንና ሽብርተኝነትን በመዋጋት መስዋዕትነት እየከፈለች የምትገኝ ሀገር መሆኗን አብራርተዋል፡፡

ከሰሐራ በታች ግዙፍ ለሆነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲሁም ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ላለው ዕድገት አስተማማኝ የባህር በር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዚህ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ባገኘው የባህር በር ጥያቄ አበክራ ስትሰራ መቆየቷንና ታሪካዊ የአንካራው ስምምነት የዚህ መቋጫ መሆኑን ለሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በውይይቱ በኢትዮጵያ የተከናወነውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ፣ ንፁህ እና አረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና ለሁለንተናዊ የቀጠናው ትብብር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያና ኪርጊስታን መካከል በሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ በቴክኖሎጅ፣ በንግድ እንዲሁም በአቪዬሽን ዘርፎች በጋራ መተባበር እንደሚገባና ለዚህም ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ገልጸዋል።

ተምሪበክ ኢርክኖቭ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነታቸውን መፍታታቸውን እንደሚደግፉ ጠቅሰው፤ ስምምነቱ በቀጣይነት በሁለቱ ሀገራት መካከል መረጋጋትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተከናወነውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እና የአረንጓዴ ልማት ክንውንን እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያና ኪርጊስታንን ትብብርን በማጠናከር የሀገራቱን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ለዚህ ስኬት ሀገሪቱን ሸፍነው ለተሾሙት አምባሳደር ሙሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.