Fana: At a Speed of Life!

በአቶ ደመቀ መኮንን የተቋቋመው “የአዳም ፋውንዴሽን” ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተቋቋመው “የአዳም ፋውንዴሽን” ይፋ ሆነ።

በሸራተን አዲስ በተከናወነው የማብሰሪያ መርሐ ግብር የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጅቶች ተወካዮች፣ አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ፋውንዴሽኑ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመተባበር የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ በማድረግ በአፍሪካ መቀንጨርን የማስቆም ዓላማ አንግቧል።

የፋውንዴሽኑ መሥራች እና የቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን÷ በመሪነት ዘመኔ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የተመጣጠነ ምግብ መሆኑን ተረድቻለሁ ብለዋል።

የአዳም ፋውንዴሽን ግብርና፣ ትምህርት፣ ማህበራዊ ጥበቃ፣ ምግብ ማቀነባበር፣ ጤናና ሥርዓተ ምግብን ማሻሻል በፕሮጀክቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የሚከናወኑ ተግባራ ተስፋ ሰጭ መሆናቸውን ገልጸው፤ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግቡን እንዲመታ ለማገዝ ፋውንዴሽኑን ለመመስረት አነሳስቶኛል ብለዋል።

በዚህም የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን በማስፋት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ብልጽግና የበኩሌን ለመወጣት በቁርጠኝነት እሰራለሁ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አምራችና የበቃ የሰው ሀይል ለመፍጠር በቅድሚያ ሥርዓተ ምግብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.