የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ፡፡
በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍሰሃ ሻወል በኒውዴልሂ በተካሄደው ዓለም አቀፉ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማህበር ጉባዔ ላይ ተሳትፈዋል።
በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግርም፥ በኢትዮጵያ ምቹ የሆኑ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሉ አብራርተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እድሎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በግብርና፣ማኑፋክቸሪንግ፣አይሲቲ፣ ማዕድንና ቱሪዝም ዘርፎች ገና ያልተነኩ እምቅ ሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ስለሆነም የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።