Fana: At a Speed of Life!

ትራምፕ ለዩክሬን አሜሪካ ሰራሽ ሚሳኤል እንድትጠቀም መፈቀዱ ስህተት ነበር አሉ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጆ ባይደን ለዩክሬን አሜሪካ ሰራሹን የረጅም ርቀት ታክቲካል ሚሳኤልን ተጠቅማ ሩሲያን እንድታጠቃ መፍቀዳቸው ስህተት ነበር ሲሉ ተችተዋል።

ትራምፕ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጆ ባይደን ይህን ከመወሰናቸው በፊት እኔን ማማከር ነበረባቸው ብለዋል።

የተሰናባቹ ፕሬዝዳንትን ውሳኔ “አይረቤ” ሲሉ ወርፈው ሊቀለብሱት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በተለይ ደግሞ የእኔ አስተዳደር ስልጣን ሊረከብ አንድ ሳምንት ሲቀረው መፈቀድ አልነበረበትም ብለዋል።

የተመራጩ ፕሬዝዳንት አስተያየት የመጣው የባይደን አስተዳደር የስልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ እርዳታ እያጧጧፉ ባለበት ወቅት ነው።

ጆ ባይደን “አርሚ ታክቲካል ሚሳኤል ሲስተም” የተባለ አሜሪካ ሰራሽ ረጅም ርቀት ሚሳኤል ተጠቅማ ዩክሬን የሩሲያን ግዛት እንድታጠቃበት ይሁንታ መስጠታቸው ይታወቃል።

ዩክሬን ሚሳኤሉን ተጠቅማ ሩሲያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢላማዎችን መምታቷም የሚታወስ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን ሚሳኤሉን እንድትጠቀም የተሰጠውን ፈቃድ ሊሰርዙት እንደሚችሉ መናገራቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.