Fana: At a Speed of Life!

የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ለወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲተላለፍ አቅጣጫ ተቀመጠ

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ለወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲተላለፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ፣ አሥተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታልን ለማቋቋም ድጋፍ ያደጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እምነት የጣሉበት ተቋም ነው ያለው ቋሚ ኮሚቴው÷ የተጣለበትን እምነት ለመረከብ ከወዲሁ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት አለበት ብሏል።

የወሎ ተርሸሪ ኬር የሕክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ቦርድ የወሎ ሕዝብ የጣለበትን አደራ እየተወጣ በመቆየቱ ቋሚ ኮሚቴው አመሥግኗል፡፡

በቀጣይም ቦርዱ እና የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ በጋራ በመሆን ለሕብረተሰቡ ግልፅ በሆነ መንገድ ሆስፒታሉን መቼና በምን ሁኔታ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያስተላልፍ የድርጊት መርሐ-ግብር አዘጋጅቶ እስከ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቅ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡

ሆስፒታሉን በማስተላለፍ ሂደት መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.