የሠላም ስምምነቱ ለሕዝቡ እፎይታ ሰጥቷል- ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ያደረገው የሠላም ስምምነት ለሕዝቡ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
ስምምነቱ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ እና የሚበረታታ ርምጃ መሆኑን የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ጋሊ ሙክታር ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠሩ የሠላም ችግሮች የዜጎችን ሕይወት አስቸጋሪ አድርገውት እንደነበር አውስተው÷ የተደረሰው የሠላም ስምምነት ሁኔታውን በመቀየር ለሕዝቡ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በቀጣይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ጥረቱ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ልዩነታቸውን በሠላም እንዲፈቱ ሁሉም አካል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው÷ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር የተደረሰው ሥምምነት ተግባራዊነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡