Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል 5 ዞኖች የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 7፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል አምስት ዞኖች ለአራት ቀናት የሚቆይ ክትባት ሊሰጥ ነው፡፡

ፖሊዮ መሰል በሽታ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ በመታየቱ ለዚህ ወረዳ አጎራባች በሆኑ የደቡብ ክልል 5 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ከመጪው አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ጀምሮ ክትባቱ ይሰጣል ተብሏል፡፡

ለአራት ተከታታይ ቀናት ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት በዘመቻ መልክ ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቋል ፡፡

ክትባቱ በኦሮሚያ ክልል ሲራሮና ሻላ ወረዳዎችም የሚሰጥት ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በደቡብ ክልል ሀዲያ፣ከንባታ ጠንባሮ፣ሀላባ፣ሲዳማና ወላይታ ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ 176 ሺህ ህጻናት ይሰጣል ሲሉ የክልሉ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና ስራ ሂደት ባለቤት አቶ እንዳሻው ሽብሩ ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው ዙር በሲዳማ ዞን ስር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ክትባቱ ይሰጣል ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ እንዳሻው በምዕራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ በአንድ የ24 ወር ህጻን ላይ ፖሊዮ መሰል በሽታ መታየቱንና ለዚህ የክትባት ዘመቻ የኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውንና ለዘመቻው ስኬት ትምህርት ቢሮዎች፣የሀይማኖት አባቶች ፣ሚዲያ፣የሴቶች ልማት ቡድን አባላት፣ሲቪክ አደረጃጀቶችና ህብረተሰቡ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ክትባቱ ከዚህ ቀደም ህጻናቱ ቢከተቡም ባይከተቡም የሚሰጥ መሆኑን ከደቡብ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.